ማህበራዊ ጉዳዮች - Social Matters

ምንያለሽ ተራ – በኄኖክ ስጦታው(አዮሃ መጽሄት ጥቅምት 2010 ዕትም)

ተራ፦ ማለት፥ ቃሉ የሸቀጥ መደብር፥ ስፍራ፥ ረድፍ የሚል ትርጓሜ ሲኖረው፤ ተረረ ከሚለው ስየመጣ ነው። የገበያ ሸቀጥ በእያይነቱ የሚሸጥበት የእህል የልብስ ወይም የልዩልዩ ሸቀጥ ዐይነት፥ የመደብር ቁጥርና የመደብር ተራ እንደሆነ አቢሲኒካ የቃላት መፍቻ ድረ–ገፅ ይነግረናል።

ምናለሽ ተራን ለመጀመሪያ ጊዜ ለሚመለከት ሰው በሰዉ ትርም ስ ውስጥ ጊዜ ምን ያህል እንደሚሮጥ ይታዘባል። ከጊዜ ጋር መሮጥ ለመጀመር ረዳት አስፈልጎኝ ነበር። ከፍጥነቱ ጋር የሚያስተዋውቀኝ ውስጥ አዋቂ፤ ምናለሽ ተራን አብጠርጥሮ መውጫና መጊያውን ጠንቅቆ የሚያውቅ ረዳቴ አማኝነት እየተመራሁ ጉብኝቴ ተጀመረ። ምናለሽ ተራ ከመርካቶ ገፅታዎች ውስጥ ትልቁን ቦታ ትይዛለች። ዙሪያዋን በብዙ ተራዎች ተከባለች። ጭድ ተራ፥ ቦንብ ተራ፥ ጎማና ተራና ሲዳሞ ተራ ያዋስኗታል። በውስጧም ብዙ ተራዎችን አቅፋ ይዛለች። ከእነዚህም ውስጥ አንዱ “ሾዴ ተራ” ይሰኛል።

“ሾዴ” ማለት ቃሉ አራድኛ ሲሆን “ሾዳ” ወይም ጫማ ነው። ሾዴ ተራ በቅርብ ጊዜያት ውስጥ ስሙን ያገኘ ተራ ይመስላል። አገልግሎት ላይ የዋሉ ጫማዎችን ከሃምሳ ብር እስከ ስ ምንት መቶ ብር ድ ረስ ታገኛለህ። ለምሳሌ፥ በመደበኛው ገበያ አስከ ሶስት ሺ ህ ብር ድረስ የሚሸመት ኦርጅናል ናይኪ ጫማ በሾዴ ተራ ግን ስድስት መቶ ብር ተጠርቶልኛል። የሚገርም ስኬቸር ጫማ ደግሞ ስምንት መቶ ብር ጥሪው ነው። በምናለሽ ተራ ውስጥ ቁርጥ ዋጋ ብሎ የገበያ ሳይንስ አይሰራም። ለአንድ እቃ እንደመነሻ የሚጠራ ዋጋም የመጨረሻው ጥሪ ላይ የሚቆመው በብዙ ንትርክና ክርክር በኋላ ነው። ምክንያቱም፥ ስምንት መቶ ብር የተባለውን ስኬቸር ጫማ በሶስት መቶ ሃ ምሳ ብር ትሸምተዋለህ።

ሾዴ ተራ የራሱ የገበያ ሰንሰለት አለው። በጠዋት ተነስተው ከተማይቱን የሚያስሱት ቁራሌዎች ለዳግም አገልግሎት ሊውሉ የሚችሉ ጫማዎችን የሚያስረክቡት እዚሁ ነው። ሁለተኛው የጫማዎቹ ምንጭ ኮንትሮባንድ ሲሆን ተደርገው ኬላን አልፈው እዚህ የሚደርሱ ናቸው። ሶስተኛው ምንጭ ደግሞ ቦንዳ ነው። ከሳልባጅ አልባሳት ጋር ወደ አገር ቤት ይገባሉ። ጫማዎቹ ለሽያጭ ከመቅረባቸው በፊት የተወሰኑ ሂደቶችን ያልፋሉ። የመጀመሪያው አጠባ ነው። ጫማ አጣቢዎች በየጥጋቱ ሆነው ያለማቋረጥ ሲሰሩ ትመለከታለህ። ሁለተኛው ደረጃ ጠጋኞች ናቸው። ይህም የታጠበው ጫማ ሲደርቅ ወደአዳሾች ያመራል። ከእድሳት በኋላ ወደ ቀለም ቀቢዎች ይደርሳል። ሾዴ ተራ የብዙ ሊስትሮዎች ስብስብ ይመስላል። ጥያቄዎቼን በመመለስ የተባበረኝና የሽያጭ ሰራተኛ የሆነው ሙዲ (መረጃውን በግልፅ ስላካፈለኝ አመሰግነዋለሁ) ስሰናበተው እንዲህ አለኝ፦ “እንግዲህ በአቅምህ እና በእግርህ ልክ ጫማ መግዛት ስትፈልግ ብቅ በል”። ሌላው በምናለሽ ተራ ውስጥ ያለው ብረት ተራ ነው። ብረት ነክ ነገር ሁሉ እዚህ ቦታ ላይ ፍዳውን ያያል። በርሜል ተቆርጦ የልብስ ማጠቢያ ሳፋ ከሚሰራው አንስቶ እስከ ከባባድ ብረቶችን አቀናብሮ የገንዘብ ካዝና የሚሰራበት ስፍራ እዚሁ ነው። ይህ ቦታ ድብልቅልቅ ያለ ጩኸት የሚወጣበት ሲሆን ታላቁ የከተማችን የድምፅ ብከላ ምንጭ መባል ያንሰዋል። አካባቢው በዚህ ኳኳታውም ቅፅል ስም አትርፏል። አፍሪካ ጃዝ መንደር ይሰኛል።

መሬት ላይ ወድቆ ቢያዩት ዋጋ የማያወጣ ቆሼ በአንድ መደብ ላይ ተከምሮ ሲሸጥ አይተህ ታውቃለህ? እኔ ግን ይህንን ጉድ ያለዛሬም አጋጥሞኝ አያውቅም። ይህ ተራ ነው ምናለሽን ምናለሽ ያስባላት። እንግዲህ እዚህ ላይ ቆም ብለን ያየሁትን እንድታይ ልጋብዝህ፦ አሮጌ ማንኪያ እና ሹካዎች፥ የማሕተም እንጨት፥ የዛገ መቀስ፥ አሮጌ ላይተር፥ የዛገ ቢላዋ፥ ያረጀ አርቴፊሻል ሞባይል (ለህፃናት)፥ አሮጌ ብረት ድስት፥ የፀሎት መቁጠሪያ፥ አሮጌ የቴፕ ክር (ካሴት)፥ ቅል፥ ተንቀሳቃሽ ስልኮችና መለዋወጫዎች፥ አሮጌ ባትሪ ድንጋይ፥ ኳስ፥ መጥረቢያና ጩቤ፣ የበር ማጠፊያና መቀርቀሪያ፥ የጄሪካን ክዳን፥ የሲሚንቶ መለሰኛ፥ ላይተር፥ አሮጌ ዣንጥላና እርጅት ያለ የሴት ቦርሳ፥ የእጅ ባትሪ፥ አሮጌ ጫማዎች፥ አርቴፊሻል አበባ፥ የድሮ ዲስኮ ሰዓት፥ ከተር፥ አሮጌ የሴቶች ቀበቶ፥ ሜትር፥ መሮ፥ መፍቻ፥ የውሻ ማሰሪያ ሰንሰለት፥ አሮጌ የሕፃን ልጅ መነፅር፥ አሮጌ ዋንጫ፥… እነዚህ ሁሉ በአንድ መደብ ላይ ተዘርግተው ለሽያጭ የሚቀርቡበት ቦታ ናት – ምናለሽ ተራ።

የምናለሽ ተራ እንቅስቃሴ ትንፋሽ ያሳጥራል። ምናለሽ ተራ እና የቁራሌዎች የጠበቀ ዝምድና የሚስተዋለው እዚህ ነው። ሁሉም ነገር ይሸጣል። ለአንዳንድ የማሕበረሰብ ክፍሎች “ቆሻሻ” ተብሎ የተወገደ ዕቃ ምናለሽ ለድጋሚ አገልግሎት ታውለዋለች። የአገልግሎት ዘመናቸውን የጨረሱ ኤሌክትሮኒክስ ተጠግነው የአገልግሎት ዘመናቸው የሚራዘመው እዚሁ መንደር ነው። የሚናቅ ስራ፥ የሚጣል እቃ የለም። “ገንዘብ እንዴት ይጣላል?” የምትል ትመስላለች- ምናለሽ ተራ።

ባለብልቃጥ ዲዮድራንቶች በተለይ ፈሳሾቹ ሲያልቁ ብልቃጣቸውን አንድ ብር ዋጋ እንዳላቸው የታዘብኩበት ቦታ ላይ ደረስኩ። ትናንሽ ብልቃጦች ተከምረዋል። ወደሻጩ ቀርቤ ራሴን አስተዋወቅኩና ጥቂት ጥያቄዎች እንዲመልስልኝ መልካም ፍቃዱን ጠየኩት፤ ተባበረኝ።

ዘመድኩን ይሰኛል። በቆራሌው ሙያ ዘርፍ አስር ዓመታት ያክል ሰርቷል። አሁንም በዚሁ ስራ የቁራሌዎች ተቀባይ ሆኖ እየሰራ ነው። መቼስ መልሰው ዲዮድራንት ሊያመርቱበት እንዳልሆነ ልቤ ቢነግረኝም በጥርጣሬ እየተናጥኩ እንዲህ ስል ዘመድኩን ጠየቅኩት።

“እነዚህን የዲየድራንት ብልቃጦች ጥቅም ምንድነው?” በማለት ላቀረብኩለት ጥያቄ የመለሰልኝ መልስ አስደንግጦኛል። “ዋንኛው አገልግሎታቸው ለምግብ ቤቶች መጠቀሚያነት የሚውሉ የጨው እቃ ይሰራባቸዋል” የጨው እቃ ለማድረግ ቀላል ነው። የዲዮድራንቱ ክዳን ሲከፈት አናቱ ላይ ያለውን ብይ ካወጣን በኋላ ክዳኑ ጨው ለመነስነስ እንዲመች በቀጫጭኑ ይበሳል። የጨው እቃ ሆነ ማለት አይደለ? – “እዝጎ!” አልኩ በሆዴ።

ያለቀ ዲዮድራንት ብልቃጥ ቁራሌዎቸ አንድ ብር ይገዙና ለምናለሽ ተራ በሁለት ብር ያስረክባሉ። ለጨው እቃ የሚያዘጋጁ ሰዎች ደግሞ በሶስት ብር ከነዘመድኩን ላይ ገዝተው አናቱን ከበሱ በኋላ ለቸርቻሪዎች በአራት ብር ለቸርቻሪዎች ያስረክባሉ። ቸርቻሪዎች ከአምስት ብር ጀም ሮ ለተጠቃሚዎች ያስረክባሉ። ይህ የንግድ መረብ አያሌ እውነታዎችን በውስጡ ይዟል። አንዱ ምግብ ቤት ገብተህ የቀረበልህ ምግብ ተጨማሪ ጨው እስንዲሰጡህ ስትጠይቅ በዲዮድራንት ብልቃጥ ሲመጣልህ አስበኸዋል? የጨው ዕቃ የሚጠቀሙ ምግብ ቤቶች ግንባር ቀደም ተጠቃሾች ናቸው። በአገሪቷ ውስጥ ያሉ እጅግ ዝቅተኛ ምግብ ቤቶች ብዛት አንፃር ከምግብ ጋር ፈፅሞ ሊዛመድ የማይችልን ቁስ እንደሆነ ማሰብና አፅንዖት ሰጥቶ ማለፉ የነገሩን ክብደት ያሳያል።

ምናለሽ ተራ የእደጥበብ መንደር ናት። እናቶች በብዛት የተሰባሰቡበት አካባቢ ላይ ደረስኩ። አገሪቱ የእንጀራ መሶብ ለካስ እዚህ ነው ያለው? እናቶች የስራ ትስስሩን አጠገብ ለአጠገብ ሆነው ይተገብሩታል። አሮጌም ሆነ አዲስ መሶብና ሌማት ከፈለግክ ሞልቷል። አክርማ፥ ስንደዶ፥ ሰበዝ ፥ በተለያዩ ቀለማት ያሸበረቁ አለላዎች እዛው በዛው ይሸጣሉ። ጎን ለጎን መሶብ የሚሰፉ እዛው አሉ። ከኤሌክትሪክ ምጣድ ሰራተኞች ረፍት አልባና ፈጣን እንቅስቃሴ ትርዒት ይመስላል። የከሰል ምድጃና የኬሮሲን ቡታጋዞች ተጠጋግነው ለዳግም አገልግሎት የሚዘጋጁትም እዚሁ ነው። ምናለሽ ተራ የጎጆ ኢንዱስትሪ መንደርም ናት። የፈጠራ ስራ ወደማሕበረሰቡ ያለምንም እውቅና የሚዳረስበት ማዕከልም ጭምር። የሞደፊክ እና እድሳት ውጤት የሆኑ ምርቶችን ለዳግም አገልግሎት ሲውሉ መመልከት አጃኢብ ያስብላል።

ለእርስዎ ፋሽኑ ያለፈበት እና አርጅቷል የሚሉት፣ ለሌሎች ግን የክት ነው

963 Comments