ልብ-ወለድ - Short Fiction

ቂም የሸፈነው እውነት – በሜሪ ፈለቀ

“መለያየት እፈልጋለሁ፡፡ ፍታኝ?” አልኩት በመኪናው መስኮት አሻግሬ ዓይኖቹን እየሸሸሁ፡፡
“እሺ!!” ነበር መልሱ:: ቢያንስ ‘ለምን?’ ብሎ እንዴት አይጠይቀኝም?
“መች ነው እንዲሆን የምትፈልጊው? አሁን? ነገ? ከሳምንት በኋላ? መቼ?” ቀለል አድርጎ ቀጠለ፡፡ ቀጥዬ የምለው ጠፋኝ፡፡ ለራሴ ምክንያት መስጠት እፈልጋለሁ፡፡ ተናዶ እንዲናገረኝ እሱ ላይ እንከን ማግኘት አጥብቄ እፈልጋለሁ፡፡’ፈታችው’ ከመባል ሌላ ቅጥያ ተጨምሮበት ‘ስላናደዳት ፈታችው’፣ ‘ስለመታት ፈታችው’……… ብቻ ምክንያቱ ከሱ ቢመጣ ደስ ይለኛል፡፡
“ካለቀልን ዛሬም ብንፋታ ደስ ይለኛል፡፡”
“ከዛሬ በኋላ ተፋተናል፡፡ የግድ በህግ መፋታት የለብንም፡፡ እኔን መፍታት አይደል የፈለግሽው? ስለወደድኩሽ እንጂ ማንም ስለፈረመ እና ምስክር ስለተጠራ አላገባሁሽም፡፡” ብሎኝ ከመኪናው ወረደ እና የኔን በር ከፈተልኝ፡፡ ቤታችን ደጅ ደርሰን ነበር፡፡ ተናደድኩ፡፡
“የንብረት ክፍፍሉ……..” አላስጨረሰኝም፡፡
“የትኛውን ንብረት ነው የምትፈልጊው?” የአጥሩን በር ከፍቶ በእጁ እንድገባ አሳየኝ፡፡
“ድርሻዬን::”
“ህምምምም…….. ቅር ካላለሽ ትንሿን መኪና ልውሰዳት ሌላውን ንብረት አልፈልገውም፡፡ ከዛሬ በኋላ ባልሽ አይደለሁም፡፡ ምንም ንብረትም የለኝም፡፡” ብሎኝ ‘ትንሿ’ ያላት መኪናው ውስጥ ገብቶ ተመልሶ ሄደ፡፡
ምን እንደምፈልግ ግራ ገባኝ፡፡ ካሳሁንን ሳላገባው በፊት ነበር የምፈታው ቀን የሚናፍቀኝ፡፡ ሳላገባው ፈትቼዋለሁ፡፡ እሱ ያገባኝ የመሰለው ቀን እኔ አግብቼም ፈትቼዋለሁ፡፡ታዲያ ለምን አገባሁት? እሱን አላገባሁትም፡፡ ገንዘቡን እንጂ። ወንዶች ‘ሴት ልጅ ገንዘብ ያለው ወንድ ትወዳለች’ ሲሉ ሳቄ ያመልጠኛል፡፡ ወይ ሰውየው ማርኳታል ወይ ገንዘቡ ማርኳታል፡፡ ለአንዳቸው ቅድሚያ ትሰጣለች፡፡ለገንዘቡ ብላ ከሆነ ገንዘቡን እንጂ እሱን አትወደውም። ገንዘቡ እስካለ ወይም የምትፈልገውን እስክታገኝ ድረስ አለች፡፡ እነሱ ግን ራሳቸውን ሳይሆን ገንዘባቸውን ያቀርቡላታል፡፡ ምክንያቱም የቁስን ያህል ራሳቸውን አያምኑትም፡፡ ስለዚህ ከቁሳቸው ይልቅ ራሳቸውን ተወዳጅ አድርገው ማቅረብ ሲሳናቸው ለገንዘቤ ብላ ነው የወደደችኝ ይላሉ እንጂ ገንዘቤን ነው የወደደችው አይሉም፡፡ ሰውየውን ከወደደችው ለገንዘቡ ብላ፣ ለቁመናው ብላ፣ ለወዙ ብላ…. የሚሉት ቀልድ አይጥመኝም፡፡ በቃ ሰውየውን ነው የወደደችው፡፡

የዛን ቀን ምሽት አልመጣም፡፡ ጠበቅኩት፡፡ እውነቱን እንደሆነ ገባኝ፡፡ ካሳሁን ፈቶኛል፡፡ ሁለተኛው ቀን መሸ ።አልመጣም፡፡ አልደወለም፡፡ ሶስተኛ ቀን ሆነ……… አራተኛ ቀን መጣ… … አስር ቀን ሞላው። አልመጣምም። አልደወለምም። የገባኝ ግን ቢመጣ ደስ እንደሚለኝ ነው፡፡እሱን መፍታት ያስደስተኛል ብዬ ያሰብኩትን ያህል አልነበረም የደስታዬ መጠን፡፡

“አልወደውም፡፡ ከሀብቱ እንጂ ከእርሱ ጉዳይ የለኝም።” ለራሴ ብቻዬን አነበነብኩ። ስልኬን እልፍ ጊዜ ልደውልለት አነሳሁ። እልፍ ጊዜ ተውኩት፡፡ በአስራአንደኛው ቀን ስልኬ ጠራ። እሱ ነበረ። ለምን ደስ አለኝ? አብሬው መኖር የማልፈልገው ሰው ድምፁን መስማቴ እንዴት አስደሰተኝ?
“ደህና አደርሽ ሰብሊ? …… ላግኝሽ?”
“እሺ:: የት እንገናኝ?”

“ስራ ቦታ:: አራት ሰዓት ላይ መጥቼ ወስድሻለሁ፡፡”
ስራ የመግባት ፍላጎት አልነበረኝም፡፡ቁምሳጥኑን ከፍቼ ሊያቆነጀኝ ይችላል ብዬ ያሰብኩትን ሁሉ ልብስ ሞከርኩ፡፡ ላማልለው? ወይስ ከሱ በመለየቴ አለመከፋቴን ለማሳየት? ለራሴ የምሰጠው ምክንያት ባይኖረኝም በሱ ፊት ቆንጆ ሆኜ መታየት ፈለግኩኝ፡፡ አምስት ዓመት በትዳር አብሬው ስኖር ይሄ ግድ ሰጥቶኝ አያውቅም ነበር። በጥንቃቄ ስዋብ ብዙ ሰዓት ፈጅቼ ደረስኩ፡፡ ተጋብተን ብዙም ሳንቆይ ነበር ካሳሁን እቤት ከምትውዪ ብሎ ለንግድ ተስማሚ የሆነ ቦታ ላይ ትልቅ የሴቶች ፀጉር ቤት የከፈተልኝ ፡፡ በሩ ላይ ሲደርስ የት ይዞኝ ሊሄድ እንደሆነ እያሰብኩ ነበር፡፡ ብዙም ግድ ያልሰጠው ሰላምታ ሰጥቶኝ የመኪናውን በር ከፍቶ አስገባኝ፡፡ በሚከብድ ዝምታ መኪናውን መንዳት ጀመረ፡፡ ላገኘው እንዳልቸኮልኩ፡፡ ተጨነቅኩኝ፡፡
“የት ነው የምንሄደው?” አፌ ይሄን ይበል እንጂ የትም ብንሄድ ግድ አልነበረኝም፡፡
“የምንጨርሰው ጉዳይ አለን፡፡”

ባንክ ቤት በር ጋ ስንደርስ በሁለታችን ስም የነበረውን የባንክ አካውንት ሊያዛውርልኝ መሆኑን ነገረኝ፡፡ በተዘባረቀ ስሜት ውስጥ ሆኜ የሚጠበቅብኝን ፈፀምኩ፡፡ እድሜውን ሙሉ የሰራው ገንዘብ መሆኑን እያወቅኩ ‘አንተስ?’ ብዬ እንኳን አልጠየቅኩትም፡፡ ነገር ዓለሙ ዞረብኝ፡፡ ምንም ሳንነጋገር ፀጉር ቤቱ በር ጋር ደርሰን፡፡በር ሊከፍትልኝ ከመድረሱ ዘልዬ ከመኪናው ወረድኩ፡፡ በሌላ ትህትናው መቁሰል አልፈለኩም፡፡
“የት ነው ያለኸው?” አልኩት
“ቤት እስካገኝ ሆቴል ነው ያረፍኩት::”
“ለጊዜው እኮ እቤት መሆን ትችላህ::”
“በሚቀጥለው ሳምንት በአንዱ ቀን የቤት ባለቤትነቱን ስም አዛውርልሻለሁ:: ሰሞኑን ስራ ስለሚበዛብኝ የምችል አይመስለኝም፡፡” ብሎኝ መኪናው ውስጥ ገብቶ ሄደ፡፡ ራሴ የሚፈነዳ መሰለኝ፡፡የማብድ የማብድ መስሎ ተሰማኝ፡፡ ወደቤቴ ሄድኩ፡፡
የደስታዬ ጫፍ ይሆናል ብዬ የማስበው ቀን ሲመጣ እርካታን ሳይሆን ባዶነትን ተሸክሞ ነው የመጣው፡፡ የምፈልገው ሁሉ ኖረኝ፡፡የማስበው ሁሉ ሰመረልኝ፡፡ ግን ትርጉም አልባ፣ ደስታ የለሽ ሙት ሆነብኝ፡፡

**************

እንደማንም ያልነበረው ልጅነቴ፡-
ሰዎች ስለልጅነታቸው ሲያወሩ ‘እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ…..’ ሲሉ እገረማለሁ:: ‘ማንኛውም ኢትዮጵያዊ’ እኔን ያቀፈ ማዕቀፍ ይሆንን?
በቀን አንዴ ትርፍራፊ ለመቅመስ መስገብገብ፣ ጎዳና ላይ በገነባቻት የላስቲክ ቤት አጠገብ ተቀምጣ የምትለምን ወፈፍ የሚያደርጋት እናት፣መለመኛ የሆኑ መንታ ታናናሽ እህትና ወንድም፣ አስር ሳንቲም ለመመፅወት የሚመፃደቅ ሂያጅ፣ በባዶ እግርና በእኩዮች ምፀት ታጅቤ የምዳክርበት ትምህርት ቤት…….. ከማንኛውም ኢትዮጵያዊ የተለየ ልጅነት ነው፡፡

ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እናቱ ልመናን ተናዛለት አባት አልባ ህፃናት መንገድ ዳር አስታቅፋው አልሞተችም፡፡
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እናቱ የሚበር መኪና ውስጥ ገብታ ስትሞት የሚሰማውን ከእብደት ያልተለየ ስሜት አያውቀውም፡፡
የኔ ልጅነት ‘እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ’ የሚባለው ማዕቀፍ ውስጥ የማይገባው ልጅነት የሚባለው ዘመኔ በአስር ዓመቴ አክትሞ የሁለት አመት ጨቅላ መንታ ታናናሾቼን እየለመንኩ ማሳደግ ግዴታዬ ስለነበር ነው። ዓለም ስትከረፋብኝ፣ በርሃብ ከሚጮሁ ታናናሾቼ ጋር ኡኡኡ ብዬ ሳለቅስ “እንደእናቷ ጠሸሸች” እተባልኩ አራት ዓመታትን ጎዳና መግፋቴ ነበር፡፡
አንድ ምሽት ታናናሾቼን አስተኝቼ ነትቦ እርቃኔን ያጋለጠውን ልብሴን እየሳብኩ ከላስቲክ ጎጆአችን ፊት ለፊት ቆሚያለሁ፡፡ መኪና ሲጢጥ ብሎ ሲቆም ሰማሁ፡፡ የሰከረ ወንድ ድምፅ ተከትሎ ተሰማኝ፡፡
“እሙዬ ነይ እስኪ……”
“ምን ፈለግክ?”
“አንቺን”
“ሸርሙጣ አይደለሁም፡፡”
“ታዲያ እዚህ ምን ይገትርሻል?”
“ቤቴ ነዋ…..” በእጄ ጠቆምኩት።
“ስንት ዓመትሽ ነው?”
“አስራ አራት” ከመኪናው ወርዶ እየተንገዳገደ ተጠጋኝ፡፡
“300 ብር እሰጥሻለሁ፡፡”
“ሸርሙጣ አይደለሁም አልኩህ እኮ……”
“ሸርሙጣ ነሽ ማን አለሽ? ጎዳና እያደርሽ ምንም አልቀመስኩም ለማለት ነው?” ከዛ በላይ ፀያፍ ቃላቶች ሰምቼ አውቃለሁ፡፡ የዛን እለት ግን ሰቀጠጠኝ፡፡ አጠገቤ ያገኘሁትን ድንጋይ አንስቼ ከፍ አደረግኩ
“በዚህ አናትህን ሳልከፍልህ ሂድ ከዚህ ጥፋ”
“ምንም የማታውቂ ከሆነ 1000 ብር እሰጥሻለሁ”

ደጋግሜ የብሩን መጠን አነበነብኩት፡፡ በህልሜ እንኳን አስቤው የማላውቅ ዓይነት ነበር፡፡ ምን ያህል ፍርሃት ቢያርደኝም ከብሩ መጠን ጋር ሲወዳደር ቀለለኝ፡፡ በዛው ቅፅበት ምን እንደማደርግ እቅድ አወጣሁ፡፡ ጭንቅላቴ እጄን አላዘዘውም፡፡ የመኪናውን በር ከፍቼ ገባሁ፡፡ ሲኦልን የዛን ምሽት አየኋት፡፡ በአለም ላይ ካሉ አስቀያሚ እና ጨካኝ ፍጥረታት መሃከል ዋነኞቹ ወንዶች መሆናቸውም የዛን እለት ገባኝ፡፡ በስቃይና በተስፋ ተሰቅዤ ሊነጋ አካባቢ ወደ ላስቲክ ቤቴ ተመለስኩ፡፡ እነ አቢን ቀሰቀስኳቸው፡፡ ዛሬ ርሃብ የለም፡፡ ልመናም የለም፡፡ ገበያ ይዣቸው ወጣሁ፡፡ ለብሰውት የማያውቁትን ልብስ ገዛሁላቸው፡፡ ካፌ ወስጄ ኬክ አበላኋቸው፡፡ ጠግበን ዋልን፡፡
በተረፈኝ ገንዘብ መንገድ ላይ ሲቆሙ የማያቸው ሴቶች የሚለብሷቸውን የመሳሰሉ አልባሳት ገዛሁ፡፡ ያደርጉታል ብዬ ያሰብኩትን አደረግኩ፡፡ ይመስላሉ ብዬ ያሰብኩትን መሰልኩ። ዘወትር ማታ ሲዖል ደርሶ መልስ የኑሮዬ አንድ ክፍል ሆነ። አሁን ገንዘብ ማግኘት ቻልኩ፡፡ እንዳቅማችን ቤት ተከራየን፡፡ እህትና ወንድሜ ትምህርት ቤት ገቡ፡፡
ወንዶችን አልወድም ገንዘባቸውን እንጂ። ከወንድነታቸው የሚተርፈኝ ስቃይና ላባቸው ነው፡፡ ገንዘባቸው ግን የማልፈውን ሲኦል ያስረሳኛል፡፡ መንገድ መቆሙን ትቼ ትልልቅ ሆቴል ውስጥ መስራት ጀመርኩ፡፡ እንደዋዛ ትልቅ ሴት ሆንኩ፡፡ ሃያ አንድ ዓመት ሞላኝ፡፡ በዚህ ወቅት ነው ካሳሁንን ያገኘሁት፡፡ የሆቴሉ ደንበኛ ነው፡፡
“ቆንጆ እኮ ነሽ እዚህ ቦታ መገኘት አልነበረብሽም::” አለኝ።
“አየህ ተፈጥሮ ቁንጅናን እንጂ የተደላደለ ህይወትን አብራ አልሰጠችኝም::” መለስኩለት።
“የዛሬ ገቢሽን ልስጥሽና እቤትሽ አርፈሽ ተኚ?”
“ይበዛብሃል::”
“እጥፍ ላድርግልሽ!!”

በራሱ መኪና እቤቴ አደረሰኝ፡፡የጠየቅኩትን ገንዘብ ሳያቅማማ ሰጠኝ፡፡ በተደጋጋሚ እንዲህ አደረገ፡፡ ከቀናት በኋላ አብሬው እንዳድር በትህትና ጠየቀኝ፡፡ እቤቱ ነበር ይዞኝ የሄደው፡፡ ከሱ ጋር ካደርኩ በኋላ ወደ ሆቴል ተመልሼ መሄድ አላስፈለገኝም፡፡ በየእለቱ ማታ እቤቱ እጠብቀዋለሁ፡፡ ሲነጋ ወደቤቴ እመለሳለሁ፡፡
እንዳገባው የጠየቀኝ ቀን እብደት የቀላቀለው ስሜት ነበር የተሰማኝ፡፡ ምክንያቱ ባል ማግኘቴ አይደለም፡፡ ባል ወንድ ነው ወንድ ደግሞ የገንዘብ ምንጭ ነው። ከዛ ያለፈ አይደለም ለኔ፡፡ ካሳሁን ብዙዎች የሚያውቁት ሀብታም ነጋዴ ነው፡፡ …… በቃ!! ብር አገኛለሁ፡፡ የትኛውም ወንድ እንደሸቀጥ የሚገዛት ሴት መሆኔ ይቀራል፣ እነ አቢዬ ያለስጋት ትምህርታቸውን ይማራሉ፣ በለውጥ ገላዬን እሰጠዋለሁ፡፡ ልቤ ያውቀዋል እንደምፈታው፡፡ ተጋባን፡፡ እህትና ወንድሜን ይዤ እኔ ገንዘብን እሱ ትዳሩን ስንጠብቅ ኖርን፡፡

*********

ሳምንታት አለፉ፡፡ ሲመቸው ለቤቱ ፕሮሰስ እንደሚመጣ ቢነግረኝም ካሳሁን አልመጣም ፡፡ አልደወለም፡፡ በቤቱ ምክንያት ቢመጣና ባየው ተመኘሁ፡፡ ቤቱ አስክሬን የወጣበት ቤት መስሎ ረጭ አለ፡፡ የቤቱ ድምቀት፡- ትልቅነቱ፣ የቀለማቱ ስብጥር፣ በውስጡ ያጨቀው ውድ እቃ አልነበረም፡፡ ሞገሱን ተገፏል፡፡ ካሳሁን የለበትም፡፡ የምግቡ ጣዕም የሰራተኛዋ ጥበብ አልነበረም፡፡ ከካሳሁን ጋር የምግብ ጠረጴዛው ላይ መታደሙ እንጂ። የእንቅልፉ መጣፈጥ የአልጋው ምቾት አልነበረም በካሳሁን እቅፍ ውስጥ ማደሩ እንጂ።
ይሄ ሁሉ የገባኝ አምስት ዓመታት ዘግይቶ ሆነ፡፡ የህይወት ዘመን ልምዴንና እውቀቴን ያስከነዳው እውነት ካሳሁን ‘ሴት ልጅ ለገንዘብህ ስትል ትወድሃለች’ ብለው እንደሚያስቡ ወንዶች አልነበረም፡፡ ገንዘቡን እንደወደድኩት እንጂ ለእሱ ግድ እንደሌለኝ ያውቃል፡፡ ራሱን እንድወደው ነበር አምስት ዓመት ሙሉ ሲጥር የነበረው፡፡ የፈለግኩትን ሁሉ እንኳን አግንቼ እሱ ከሌለበት ባዶ መሆኑን ነበር ያሳየኝ፡፡ እድሜውን ካፈራው ንብረት እንደበለጥኩበት አሳይቶኝ እድሜዬን ሙሉ የጓጓሁለት ሀብታምነት ከንቱ መሆኑን ነገረኝ፡፡ አብሬው ስኖር ያላየሁት እውነት ያ ነበር፡፡
“ ማንም የኔን ያህል አውቆሽ አያውቅም፡፡” ይለኝ ነበር ሳበሳጨው፡፡ አሁን ነው ምን ያህል እንደሚያውቀኝ የገባኝ፡፡ ባዶነቴ በፍቅር እንጂ በገንዘብ እንደማይሞላ ያውቅ ነበር፡፡
ስልኬን አንስቼ ደወልኩለት፡፡

“ሰብሊ ይቅርታ ደንበኞች እያናገርኩ ነው፡፡ ቆይቼ እደውላለሁ፡፡” ብሎኝ ስልኩን ዘጋው፡፡ ‘ቆይቼ’ ያለው ሰዓት ዘላለም መሰለኝ፡፡ ሲሊፐር እንዳጠለቅኩ ተነስቼ ከቤት ወጣሁ፡፡ እንዲህ ላብድ የሚመስለኝ ሰዓት እብደቴን የማስታግሰው እህትና ወንድሜ ጋር ስሆን ነበር፡፡ አሁን እነሱ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች ናቸው፡፡ እንድረብሻቸው አልፈልኩም፡፡ በቀስታ እየተራመድኩ ማሰብ ጀመርኩ፡፡ አሁን ያለኝን ሁሉ አጥቼ ካሳሁንን ብቻ ማግኘት ተመኘሁ፡፡ እግሬን ጭንቅላቴ አላዘዘውም፡፡ ወደካሳሁን ቢሮ ሮጥኩ። ርቀቱ፣ አለባበሴ፣ የፀጉሬ መንጨፍረር…….. ምኑም ግድ አልሰጠኝም፡፡ ትንፍሼ ቁርጥ ቁርጥ እያለ በሩን ከፍቼ ገባሁ፡፡ ሁኔታዬ ያስደነገጣት ፀሃፊው መውጣቱን ነገረችኝ፡፡ በደከመ ነፍሴ ወደቤቴ ማዝገም ጀመርኩ፡፡ የመጣሁት መንገድ ርቀቱ የታወቀኝ አሁን ነው። ብዙ መንገድ ሮጫለሁ፡፡ መንገዱ ዳር ድንጋይ ላይ ተቀመጥኩ፡፡ ለብዙ ቀናት የረባ ምግብ ያለመብላቴን፣ እረፍት ያለው እንቅልፍ ያለመተኛቴን አሁን ነው ያስታወስኩት፡፡ ላዳ ይዤ ወደቤቴ ሄድኩኝ፡፡ በሩ ላይ የካሳሁንን መኪና ቆሞ ሳየው
‘እሪሪሪሪሪ……’ ማለት አማረኝ፡፡

በሩጋ ስደርስ እሱ እየወጣ ነበር፡፡ ከላይ እስከታች እያስተዋለኝ “ስደውልልሽ አታነሺም?”
“ስልኬን ጥዬው ነው የወጣሁት፡፡ ቢሮህ እኮ ሄጄ…..”
“አሁን መጥታ ነበር ሲሉኝ ነው ወደቤት የመጣሁት። ሰላም አይደለሽም?” ይዞኝ የመጣው ታክሲ ጥሩንባውን አስጮኸው፡፡

“አልከፈልሽውም እንዴ?” ብሎ እጁን ኪሱ ውስጥ እየከተተ ወደታክሲው አመራ፡፡ በዛው የማይመለስ መሰለኝ፡፡ ድጋሚ ለሳምንታት የማላየው መሰለኝ፡፡ ምን እንዳደረግኩ የገባኝ ካደረግኩት በኋላ ነው፡፡ አፌን ጭንቅላቴ አላዘዘውም፡፡
“እሪሪሪሪሪሪ…….” ብዬ አቀለጥኩት፡፡ በታክሲውና በኔ መሃከል ባለ እኩል እርቀት መሃል ደንግጦ ዞረ፡፡

“ምን ሆንሽ?” አጠገቤ ዘሎ ደረሰ፡፡ ምን እንደምለው ግን ግራ ገባኝ፡፡ የእንባዬ ጠብታ መሬቱ ላይ ተከታተለ፡፡ ባለታክሲው በጩኸቴ ተደናግጦ መውረዱን ሳይ ደነገጥኩ፡፡
“ምንም አልፈልግም፡፡ ሁሉም ይቅርብኝና አትሂድብኝ!!” እንባዬን እየታገልኩ ያወጣሁት ቃል ይሄ ነው፡፡

“አልሄድኩም እኮ ታክሲውን ልሸኘው ነው::”
“አልፈልግም እኮ ነው የምልህ፡፡ ቤቱንም ብሩንም ምኑንም አልፈልግም፡፡”
አምባረቅኩኝ፡፡ ያልኩት እንዳልገረመው ፤ እንዲህ እንደሚሆን እንደሚያውቅ ሁሉ ፈገግ እንደማለት ብሎ ወደታክሲው ሹፌር ፊቱን አዞረ፡፡ መሬት ላይ እየተንከባለልኩ መጮህ አማረኝ፡፡ ብሩን ሰጥቶት ሲመለስ በእንባ በተጋረደ ዓይኔ አየዋለሁ፡፡

“ላቆሰልኩህ ቁስል በሌላ በፈለግከው ነገር ቅጣኝ እባክህ ትተኸኝ አት….” ያልኩትን የሰማ አይመስልም፡፡ አጠገቤ ከመድረሱ ከንፈሮቼን ጎረሳቸው።
አምስት ዓመት ሙሉ እንዲህ ነበር የሳመኝ?

4,374 Comments